ከአሜሪካ ጥቃት ሊሰነዝርብኝ ይችላል በሚል ስጋት ኢራን ከኑክሌር ተቋማቷ አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎቿን የአዮዲን እንክብሎችን እያደለች እንደሆነ ተገለጸ‼️
ከአሜሪካ የግማሽ ዘመን (Midterm) ምርጫ በኋላ ሊሰነዘር ይችላል የሚባለውን የአሜሪካ ወታደራዊ ጥቃት ስጋት ተከትሎ፣ ኢራን በኑክሌር ተቋማቷ አቅራቢያ ለሚኖሩ ህብረተሰብ ክፍሎች የአዮዲን እንክብሎችን እያደለች እንደሆነ ተዘግቧል። የብሪታንያው "ዘ ታይምስ" ጋዜጣ ስማቸውን ለመጥቀስ ያልፈለጉ የኢራን ጤና ሚኒስቴር ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ባለስልጣናት በኑክሌር ተቋማት ዙሪያ በ2 እስከ 3 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ለሚኖሩ ነዋሪዎች የጨረር አደጋን ለመከላከል እንደ ጥንቃቄ እንክብሎቹን እያደሉ ይገኛሉ። ዘገባው አሜሪካ ናታንዝ አቅራቢያ በሚገኘውና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት የ"ፒክአክስ ማውንቴን" ተቋም ላይ ጥቃት ጥላ ይሆናል የሚለውን ስጋትም አንስቷል። ይህ የተባለው ዝግጅት እየተደረገ ያለው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል አዲስ ማስጠንቀቂያ ከሰጡ በኋላ በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል ያለው ውጥረት እንደገና ባነሰረበት ወቅት ነው። ሆኖም የኢራን ጤና ሚኒስቴር ከዘ ታይምስ ጋዜጣ ጋር የተነጋገረ ምንም አይነት ባለስልጣን እንደሌለ በመግለጽ ለሚኒስቴሩ የተሰጡትን መግለጫዎች ሐሰት ናቸው ሲል አስተባብሏል። እንክብሎችን የማደል መርሃ ግብር መከናወኑም በተናጠል የተረጋገጠ ነገር የለም። የአዮዲን እንክብሎች ታይሮይድ እጢን ከሬዲዮአክቲቭ አዮዲን ጨረር ለመከላከል የሚረዱ ቢሆንም፣ ሰውነትን ከሌሎች የጨረር አይነቶች ወይም ከኑክሌር ፍንዳታ አደጋ የመጠበቅ አቅም የላቸውም።