“የዓባይ ጉዳይ ተዘግቷል፤ አሁን ትኩረታችን የባህር በር ነው” – ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)
ኢትዮጵያ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በማጠናቀቅ ትኩረቷን ወደ ቀይ ባህር የባህር በር ጥያቄ ማዞሯን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ። ሚኒስትሩ ከኤፍኤምሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ “ኢትዮጵያ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በማጠናቀቅ የዓባይን ጉዳይ ዘግታ አጀንዳዋን ወደ ቀይ ባህር አዙራለች” ብለዋል። ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግድቡን በመገንባት ያገኘችው ውጤት የባህር በር ጥያቄዋን ለማንሳት መነሻ ሆኗታል። በዓባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም ግብጽ ስታደርግ የቆየችው ጥረት ሀገሪቱ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ እንድታልፍ እንዳደረጋትም ጠቅሰዋል። ግብጽ አሁንም በዓባይ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዳደረገች የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ከማደናቀፍ ይልቅ ልትደግፍ እንደሚገባት ተናግረዋል። ይህንንም አቋማቸውን በመግለጽ፣ “የዓባይ ጉዳይ ተዘግቷል፤ አሁን ትኩረታችን የባህር በር ነው” ብለዋል። የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከኢኮኖሚያዊ ፍላጎት፣ ከንግድ ተደራሽነትና ከአገራዊ ጥቅም ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሲሆን፣ በክልሉ ያለው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሁኔታም የጥያቄውን አቅጣጫ ከሚወስኑ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል።