← All news
News Nov 7, 2026 · 14h ago

“ስልጣኔን በመልቀቅ ህይወቴን ለክርስቶስ እሰጣለሁ!” – የኡጋንዳ ጦር አዛዥ ሙሁዚ ካይኔሩጋባ

የኡጋንዳ የመከላከያ ኃይሎች አዛዥ (CDF) ጄነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ከወታደራዊ ከፍተኛ ኃላፊነታቸው በቅርብ ወራት ውስጥ ለመልቀቅና ሕይወታቸውን ለክርስቶስ ለማዋል ያላቸውን ዕቅድ ይፋ አድርገዋል። ጄነራል ሙሁዚ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልእክት፣ “የአዛዥነት ዘመኔ እያበቃ ነው። እግዚአብሔር የሰጠኝን ተልዕኮዎች ፈጽሜያለሁ። በጥቂት ወራት ውስጥ ይህንን ቢሮ ለብቁ ወታደራዊ መኮንን አስረክባለሁ፤ ከዚያም ሕይወቴን ለክርስቶስ እሰጣለሁ” ብለዋል።  ጄነራሉ ከኃላፊነታቸው መልቀቅ በኋላ ከሕዝብ እይታ ሙሉ በሙሉ እንደማይሰወሩ የገለጹ ሲሆን፣ በተጨማሪም በኡጋንዳ የመከላከያ ኃይል (UPDF) ውስጥ የሚያገለግሉ ወታደሮች ደመወዝ ወደ 2 ሚሊዮን የኡጋንዳ ሺሊንግ እንዲያድግ ጥሪ አቅርበዋል። የወታደሮች የመኖሪያ ሁኔታና ደመወዝ ማሻሻል ከቀጣይ ትኩረቶቻቸው መካከል መሆኑንም ጠቁመዋል።  ጄነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ ሲሆኑ፣ በመጋቢት 2024 የኡጋንዳ የመከላከያ ኃይሎች አዛዥ ሆነው ተሾሙ። በወታደራዊ አመራርና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያስተላልፏቸው መልእክቶች በአፍሪካ ክልላዊ ፖለቲካ ውስጥ ተደጋጋሚ ትኩረት የሚስቡ ሰው ናቸው።