የትምህርት ዘመኑ ሳይጠናቀቅ የቀጣይ ዓመት ቅድመ ምዝገባ የሚያካሂዱ ትምህርት ቤቶች ላይ እስከ አንድ ዓመት እገዳ የሚጥል ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ!
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት የቀጣይ ዓመት ምዝገባ ማካሄድ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን እና ይህንን ህግ በመተላለፍ አስቀድመው ተመዝጋቢዎችን የሚቀበሉ ተቋማት ላይ እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ የዕውቅና እገዳ የሚጥል አዲስ ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጅቷል። አሐዱ ሬዲዮ የተመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ያዘጋጀው “የአጠቃላይ ትምህርት የእውቅና ፍቃድና እድሳት አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያ ማንኛውም የአጠቃላይ ትምህርት ተቋም የትምህርት ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት የቀጣይ ዓመት የአዲስም ሆነ የነባር ተማሪዎች ምዝገባ ማካሄድ ፈጽሞ የተከለከለ ነው። በረቂቅ መመሪያው ማንኛውም የአጠቃላይ ትምህርት ተቋም የትምህርት ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት የቀጣይ ዓመት የአዲስም ሆነ የነባር ተማሪዎች ምዝገባ ሲያካሂድ ከተገኘ በመጀመሪያ በቃለ ጉባኤ በፍቃድ ሰጪው አካል ምክር ይሰጠዋል።。 በዚህ ካልተመለሰ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ማረም ካልቻለ ወይም ካላስተካከለ ለ1 ዓመት እውቅና ፈቃዱ ይታገዳል።በዚህ መልኩ የታገደ ተቋም የቅጣት ጊዜውን ካጠናቀቀ በኋላ ለቢሮው ማስተካከሉን ሲያመለክትና መስተካከሉ ሲረጋገጥ እገዳው እንደሚነሳ ተመላክቷል። ሆኖም ችግሩ ያልተስተካከለ ከሆነ የዕውቅና ፈቃዱ ሙሉ በሙሉ የሚሰረዝ ይሆናል። በተጨማሪም ረቂቅ መመሪያው ትምህርት ቤቶች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ዋና ዋና ኃላፊነቶችን እና ክልከላዎችን ደንግጓል።በዚህም መሰረት ተቋሙ ተማሪዎችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የመቀበል ግዴታ ያለበት ሲሆን ከክፍል ክፍል መዘዋወርና አለመዘዋወር ፣ አማካይ ውጤት ፣ ሪፖርት ካርድ ፣ የተገለጸ የጠባይ ደረጃ ወይም ቅድመ ቅበላ ፈተናዎችን መሰረት አድርጎ በልጆች ላይ ግዴታ መጣል የለበትም። የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርትን ወይም ሌሎች ማጠናከሪያ ትምህርቶችን ምክንያት በማድረግ ከመደበኛ የትምህርት ካላንደር ውጪ መደበኛ ትምህርት መስጠት የተከለከለ ነው። የክረምት ሆነ ማጠናከሪያ ትምህርትን ምክንያት በማድረግ በማንኛውም ሁኔታ ተማሪን ከትምህርት ገበታ ውጪ ማድረግ ፣ ለፈተና እንዳይቀመጡ ማድረግ እና ምዝገባ መከልከል ፍጹም የተከለከለ መሆኑ በረቂቅ መመሪያው ተመላክቷል።የከተማዋ ትምህርት ቢሮ በአሁኑ ወቅት በረቂቅ መመሪያው ላይ አስተያየቶችን እየሰበሰበ ይገኛል።Via Ahadu