የጥራት ጉድለት የታየባቸው ኮንዶሚኒየሞች ሊታደሱ ነው
ከ1997- 2007 ዓ.ም ባለዉ ጊዜ ውል ተይዞላቸዉ ከተገነቡና አገልግሎት እንዲሰጡ ከተደረጉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል በተወሰኑ ህንፃዎች ላይ የጥራት ጉድለት መታየቱን ተከትሎ፣ ነዋሪዎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይፈጠር የሙያዊ እርምት ሥራ ሊደረግ መሆኑን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ። ኮርፖሬሽኑ ከ1997-2007 ዓ.ም ድረስ በተገነቡ ሕንፃዎች ላይ የታዩ የግንባታ ጥራትና መሰል ችግሮችን ለመለየት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ማካሄዱን ገልጿል። በጥናቱ የችግሮቹ ዓይነትና ደረጃ ተለይቶ ቅድሚያ የእርምት ርምጃ የሚያስፈልጋቸው ሕንፃዎች ተለይተዋል። በዚህም ከነዋሪዎች ጋር በመግባባት ፣ የሥራ ተቋራጮችን በመመደብ የማስተካከያ ሥራዎችን ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አመልክቷል።