← All news
News Nov 6, 2026 · 2d ago

በመቐለ ከተማ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከዛሬ ጀምሮ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ።

“ህጋዊ ፍቃድ የሌለው” የጦር መሳሪያ የያዙ አሊያም በቤታቸው የደበቁ የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ ለትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲያስረክቡም ከዛሬ ጀምሮ የሶስት ቀናት ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸዋል። የሰዓት እላፊውን እና የጦር መሳሪያ የማስረከቡን ቀነ ገደብ በከተማይቱ መጣሉን ያስታወቀው የመከላከያ ሰራዊት ነው። በትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን ምሽቱን በትግርኛ ቋንቋ የተሰራጨው የሰራዊቱ መግለጫ፤ እነዚህ እርምጃዎችን መተግበር ያስፈለገው የመቐለ ከተማን “ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ” እንደሆነ አመልክቷል። የመቐለ የጸጥታ ሁኔታ “በሂደት መሻሻሎች እያሳየ” መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፤ ሆኖም የከተማይቱ ነዋሪዎች “አልፎ አልፎ” ለተለያዩ “የደህንነት ስጋቶች እየተጋለጡ” መሆኑን አስታውቋል። እነዚህ ስጋቶች የመነጩት ከዚህ በፊት በተለያዩ መንገዶች “ከእስር የተፈቱ ግለሰቦች” እና “የተደራጁ የዝርፍያ ቡድኖች” በሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ምክንያት እንደሆነም መግለጫው ጠቁሟል። ከጥቅምት 27 ቀን ጀምሮ ከምሽቱ 2:00 ሰዓት እስከ ጧቱ 12:00 ሰዓት ድረስ ማንኛውም ተሽከርካሪ ፣ ነሞተር ሳይክል እንዲሁም ከባድ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ውስጥ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው። ሆኖም በልዩ ምክንያት በምሽት ወደ ከተማዋ የሚገቡ ሀገር አቋራጭ ከበደ ተሽከርካሪዎች በልዩ ሁኔታ ይታያሉ ተብሏል።