ኢቦላ እንዳይገባ በቦሌ ኤርፖርት ምርመራ ተጀመረ‼️
የኢቦላ ቫይረስ ወደ ሃገር እንዳይገባ ለመቆጣጠር በመግቢያና መውጫ በሮች እንዲሁም በቦሌ ኤርፖርት የ24 ሰዓት የምርመራና ልየታ ባለሙያዎች ተሰማርተው እየተሰሩ መሆኑ ተነገረ። በአለም ጤና ድርጅት (WHO) አማካኝነት በቅርቡ "ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነ የህዝብ ጤና አስቸኳይ አደጋ" በሚል የተፈረጀው የኢቦላ ቫይረስ ’’ቡንዲ ቡጉዩ’’ የተሰኘና ከተለመደው የተለየ የኢቦላ ቫይረስ ነው። በጎረቤት ኬንያ እስካሁን 9 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 2ቱ ህይወታቸው አልፏል ተብሏል። ቫይረሱ ጎረቤት ሃገር ኬንያ መድረሱን ተከትሎ ወደ ሃገር እንዳይገባ ምን እየተሰራ ነው? ያልናቸው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ ሀብቴ፤በአየር ማረፊያዎች እና በየብስ ድንበሮች (በተለይም ከኬንያ ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች) ላይ የ24 ሰዓት የጤና ቅኝትና የሙቀት ልኬት ምርመራ እየተከወነ መሆኑን ነግረውናል። ለመሆኑ እንዲህ በድንገት ለሚከሰቱ ወረርሽኞች ወይም አደጋዎች አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት እንደሃገር ምን ዝግጁነት አለ? ያልናቸው በኢንስቲትዩቱ የአደጋዎች ዝግጁነት ዳይሬክተሯ ነኢማ ዘይኑ በቅርቡ የማልበርግ ቫይረስን የተቆጣጠርንበት ፍጥነት የመከላከል አቅማችን እየዳበረ መምጣቱን ያየንበት ነው ብለዋል፤ለሚከሰቱ የጤና ስጋቶች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ የተለያዩ የድንገተኛ እንዲሁም ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ ባለሙያዎችን አቅም ከመገንባት ጀምሮ አስፈላጊ ግብዓት እየተዘጋጁ ነው ሲሉም አስረድተዋል። እንደ ኢቦላ ያሉ ድምበር ተሻጋሪ የወረርሽኝ ስጋቶችን ጨምሮ በድንገት የሚከሰቱ በሽታዎች፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶችን ተከትለው የሚመጡ 36 ያህል የማህበረሰብ ጤና ስጋቶች ተለይተዋልም ተብሏል፡፡ የመቆጣጠርና የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በኢንስቲትዩቱ የአደጋዎች ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ነኢማ ዘይኑ ነግረውናል፡፡ ወረርሽኞችን በመከላከል በአለም የጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት የላቀ ብቃት በማሳየታቸው ለ250 የኢትዮጵያ ድንገተኛ ህክምና ቡድን አባላት ከሰሞኑ በWHO እውቅና ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ ሸገር ሬዲዮ