የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር በትእምት የባለአደራ አመራሮች ላይ የእግድ ውሳኔ አስተላለፈ።
ባለአደራ አስተዳደሩ ጥቅምት 24 በፃፈው ይፋዊ ደብዳቤ የእግድ ደብዳቤ፣ " የትእምት ባለ አደራ አመራሮች እና በርካታ ከፍተኛ አመራሮች ስራውንና ሰራተኛን ጥለው ሕገ-ወጥ ቡድን ደግፈው ራሳቸውን ከስራ አግልለዋል " ብሏል። ስለሆነም የተለየ ውሳኔ ወይም መምሪያ እስከሚሰጥ ድረስ ሁሉም የባለአደራ አመራሮች ትእምት ወክለው ማንኛውም ህጋዊ ስራ እንዳይሰሩ ማገዱን አስታውቋል። ባለ አደራ አመራሩ የፃፈው የእግድ ደብዳቤ ለሁሉም የትእምት የባለ አደራ ቦርድ አመራሮች ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ወጋገን ፣ አንበሳ ፣ አቢሲንያ ፣ አዋሽ ባንኮች እንዲሁም ለደደቢትና አደዳይ ማይክሮፋይናንሶች በግልባጭ አስታውቋል። ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት አድርጎ የተመሰረተው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ጊዚያዊ አስተዳደርና በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል ተከትሎ በትእምት አመራሮች መኃል ከፍተኛ ስም መጠፋፋት ፣ መወነጃጀል ፣ አንዱ ሌላውን የማገድ ሁኔታዎች የሚያመለክቱ በርካታ ዘገባዎች ስናቀርብ መቆይታችን ይታወሳል።