በአዲስ አበባ በቦታ ጥበት ምክንያት አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በአንድ ጉድጓድ እስከ አምስት አስከሬን መቅበር መጀመራቸው ተሰማ
በአዲስ አበባ ከተማ ያለው ከባድ የመቃብር ቦታ እጥረት ነዋሪዎችን እና የሃይማኖት ተቋማትን ፈታኝ ሁኔታ ላይ ጥሏል። ፊደል ፖስት ዌንጌት በሚገኘው የጴጥሮስ መቃብር ስፍራ ባደረገው ምልከታ፣ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እስከ አምስት ድረስ አስከሬን የመቅበር ልማድ እየተስፋፋ መሆኑን ተመልክቷል። በተመሳሳይ መልኩ በአማኑኤል ቤተክርስቲያንም ይህ አሰራር ተግባራዊ መደረጉ ተሰምቷል። በዚህም መሰረት አብያተ ክርስቲያናቱ አንድን አስከሬን ከሌላው በክዳን እየለዩ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እስከ አምስት አስከሬን በመቅበር ላይ ይገኛሉ። ጉድጓዶቹ ሙሉ በሙሉ ሲሞሉ በውስጣቸው ለተቀበሩ ሰዎች ማስታወሻ የሚሆን አጭር ሃውልት እየተተከለባቸው ይገኛል። የከተማዋ ፈጣን የህዝብ እድገትና የቦታ ውስንነት የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ በአጽንኦት እየተነገረ ነው።