ከደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ደንብ ጋር በተያያዘ 88 ሰዎች እያንዳንዳቸው 2 ሺህ ብር ተቀጡ
በአዲስ አበባ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻን በአግባቡ ባለማስወገድ ደንብ በተላለፉ 88 ሰዎች ላይ እያንዳንዳቸው 2 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት መጣሉን የከተማዋ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አስታወቀ። የባለሥልጣኑ የደንብ መተላለፍ ክትትል፣ ቁጥጥርና እርምጃ አወሳሰድ ግብረ ኃይል ባለሙያ አስናቁ አያው ለአሐዱ እንደገለጹት፣ እርምጃው የተወሰደው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድን የሚመለከተውን ደንብ ቁጥር 167/2016 በመተላለፋቸው መሆኑን ገልጸዋል። ቅጣቱ በ90 ቀናት ውስጥ የተፈጸሙ የደንብ ጥሰቶችን ተከትሎ የተጣለ ሲሆን፣ ከመኖሪያ ቤት ፊት ለፊት ባለው የ5 ሜትር ርቀት አካባቢ ጽዳትን ባለመጠበቅና ፈሳሽ ቆሻሻን ያለአግባብ በማስወገድ ደንቡን የጣሱ ሰዎች በቅጣቱ እንደተካተቱ አስረድተዋል። ከማኅበረሰቡ በሚቀርቡ ጥቆማዎችና በምስል በተደገፉ ማስረጃዎች በብልሹ አሠራር ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችን ለመለየትና ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፥ በደንብ ማስከበር ሥራው ላይ ብልሹ አሠራር የሚፈጽሙ የተቋሙ ሠራተኞችን ለመቆጣጠር ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ አስናቁ አያው ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት በብልሹ አሠራር የሚሰማሩ የተቋሙ ሠራተኞች ቁጥር መቀነሱን አመልክተዋል።