← All news
News Nov 5, 2026 · 3d ago

የጥቅምት ወር የዋጋ ግሽበት 14.6 በመቶ ደረሰ‼️

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የጥቅምት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 14.6 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም በመስከረም ወር ከተመዘገበው 11.6 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል። በወሩ የምግብና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች የዋጋ ግሽበት 14.1 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ለዚህ ጭማሪ በዋናነት አስተዋጽኦ ያደረጉት የስኳር፣ ማር እና ቸኮሌት በ36.2 በመቶ፣ የሥጋ በ23.8 በመቶ፣ የዘይትና ቅቤ በ20.6 በመቶ፣ የወተት ተዋጽኦዎችና እንቁላል በ20.1 በመቶ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ በ11.1 በመቶ የዋጋ መናር መሆናቸው ታውቋል። በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆነው የዋጋ ግሽበት 15.4 በመቶ መድረሱ ተገልጿል። በዚህ ዘርፍ የአልኮል መጠጥና ትምባሆ በ18.92 በመቶ፣ ትራንስፖርት በ17.1 በመቶ፣ ትምህርት በ15.5 በመቶ እንዲሁም ሆቴልና ምግብ ቤቶች በ11.1 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል።