← All news
News Nov 5, 2026 · 3d ago

ጠበቆች የሂሳብ መዝገብ እንዲይዙ በተጣለዉ ህግ መሠረት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጠ

በተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ 1395/2017  ባስቀመጠዉ ህግ ጠበቆችን ጨምሮ የሙያ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሂሳብ መዝገብ መያዝን አስገዳጅ አድርጓል። የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር በ2018 የግብር ዘመን በጠበቆች ላይ የሂሳብ መዝገብ ባለመያዝ እየተጣለ ያለዉ አስተዳደራዊ ቅጣት እና የግብር አወሳሰን በተመለከተ ቅሬታዉን ማቅረቡ ይታወሳል። የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ እየቀረቡ የነበሩ ቅሬታዎችን ተንተርሶ በግብር ዘመኑ ንግድ ፍቃድ  ሳይኖራቸዉ በሙያ ፍቃድ ሲሰሩ የነበሩ ባለሙያዎች የሚስተናገዱት የግብር ስሌት አሰራር ማዘጋጀቱን አሳዉቋል። በሙያ ፈቃድ ብቻ ሲሰሩ የነበሩ ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ ባላቀረቡበት ሁኔታ ከአጠቃላይ ገቢያቸው ላይ 35 በመቶው እንደ ወጪ ታስቦ ቀሪው 65 በመቶ ደግሞ ግብር የሚከፈልበት ገቢ እንደሆነ ተቆጥሮ ግብራቸው እንዲሰበሰብ እንደሚደረግም አስቀምጧል። የኢትዮጵያ የፌደራል ጠበቆች ማህበር ቅሬታዉን መሠረት በማድረግ በግብር ዘመኑ የተሰጠዉ የአሰራር ማስተካከያ በበጎ መመልከቱን ገልፆል። ሆኖም ይህ የአሰራር ማስተካከያ ለ2018 የግብር ዘመን ማሳወቂያ ብቻ ተፈፃሚ የሚሆን እንደሆነ ታዉቆ ሙያተኞች ለቀጣይ የግብር ዘመናት አስፈላጊዉ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የፌደራል ጠበቆች ማህበር የጠበቆች የሙያ ወጪ አያያዝ መመሪያ እንዲወጣ ጥረት እያደረገ መሆኑን አሳዉቋል።