← All news
News Nov 5, 2026 · 3d ago

“ከእንግዲህ በኋላ በጦርነት የሚመለስ የትግራይ ጥያቄ የለም፤ በሰላማዊ መንገድ የሚመለስ ግን ብዙ አለ”- ሌተናል ጀነራል ፃድቃን

ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ከTBS ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ የትግራይ ህዝብ ከዚህ በፊት የተሸከመው ችግርና መከራ እንዳሳዘናቸው ገልጸው፣ ከእንግዲህ በኋላ የትግራይ ጥያቄዎች በጦርነት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ማግኘት እንዳለባቸው ተናገሩ። ጄነራሉ በቃለ መጠይቁ የህወሓትን ሚና በትግራይ ህዝብ ላይ እንደ ጭነት ማሳረፋቸውን በመግለጽ፣ “ተሳስተናል፤ አሁን አውርደነዋል። ይህ ትልቅ ድል ነው” ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሚቀሩ ጉዳዮች ቢኖሩም በእርግጠኝነት ስኬታማ እንደሚያደርጉአቸው አስታውቀዋል። “ይህ ጊዜ የልጆቼና የታናናሽ ወንድሞቼና እህቶቼ ጊዜ ነው” ያሉት ፃድቃን፣ ከዚህ በኋላ ከማንኛውም የተደራጀ ኃይል ጋር ተሰልፈው እንደማይታገሉ ገልጸዋል። ሆኖም ትግራይ በምትፈልጋቸው የምክርና የእርቅ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ጄነራሉ የትግራይ ህዝብ የሚያስፈልገው ሰላም፣ እርቅና ዘላቂ መፍትሔ መሆኑን በማመልከት፣ በጦርነት የሚመለስ ጥያቄ እንደሌለና በሰላማዊ መንገድ ግን ብዙ የሚፈቱ ጉዳዮች እንዳሉ አስረድተዋል።