← All news
News Nov 4, 2026 · 3d ago

በብር ጌጣጌጥ ምርቶች ውስጥ ለካንሰር በሽታ ሊያጋልጥ የሚችል መርዛማ ኬሚካል መገኘቱ ተገለጸ።

በበይነ መረብ ገበያዎች ላይ እውነተኛ የብር ጌጣጌጦች ናቸው ተብለው የሚሸጡ ምርቶች ውስጥ ካንሰርን ሊያስከትል የሚችል ካድሚየም የተባለ መርዛማ ኬሚካል መገኘቱን ቢቢሲ በምርመራ ዘገባው አስታውቋል። በተለያዩ የበይነ መረብ ገበያዎች ላይ እውነተኛ የብር ጌጣጌጦች ናቸው ተብለው ከተሸጡ 25 ምርቶች ውስጥ ስምንቱ ከሕጋዊው ገደብ በላይ የሆነ ይህን መርዛማ ኬሚካል እንደያዙ ተረጋግጧል ሲል ዘገባው አክሏል። በአማዞን፣ ኢቤይ፣ ቴሙ፣ ኤትሲ እና ኦንባይ በተባሉ የበይነመረብ ገበያዎች ላይ የተገዙ 25 የተለያዩ የጌጣጌጥ ዕቃዎችን ያካተተ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ እውነተኛ የብር ጌጣጌጥ መሆናቸው የተረጋገጠው ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን የምርመራው ውጤት አመልክቷል። ካድሚየም ካንሰርን ከሚያስከትሉ ኬሚካሎች መካከል ተጠቃሽ ሲሆን፣ በተለይም በመተንፈስ ወይም በመዋጥ ወደ ሰውነት ውስጥ ከገባ ለጤና ከባድ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ በምርመራው የተገኙት አንዳንድ ጌጣጌጦች ትክክለኛ  የብር ምልክት ቢኖራቸውም፣ በተግባር የብር ይዘታቸው ከምልክቱ ጋር የማይጣጣሙ መሆናቸው ታውቋል።እውነተኛ የብር ጌጣጌጥ ቢያንስ 92.5 በመቶ ብር መያዝ ቢኖርበትም፣ አንዱ የብር ይዘት 8.9 በመቶ ብቻ ሆኖ ተገኝቷል። የምርመራውን ውጤት ተከትሎ አማዞን፣ ኢቤይ፣ ቴሙ እና ኦንባይ በምርመራው የተለዩትን ምርቶች ከገበያ ማስወገዳቸውን እና ለተጎዱ ደንበኞች ገንዘብ የመመለስ ሂደት መጀመራቸውን ሲያሳውቁ፣ ኤትሲ ግን ለቢቢሲ የቀረበለትን ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም። የምርመራው ውጤት በበይነ መረብ የሚሸጡ የጌጣጌጥ ዕቃዎች ጥራትና ደህንነት ላይ ከባድ ጥያቄን እንዳስነሳ ተገልጾ ሸማቾች የሚገዙትን ምርት እውነተኛነትና የደህንነት ማረጋገጫ መረጃ ማጣራት እንዳለባቸው መረጃው አስገንዝቧል።