በኢትዮጵያ ስትሮክ ከሦስት እስከ አምስተኛ ደረጃ አሳሳቢ ተብለው ከተቀመጡት በሽታዎች ውስጥ ይገኛል ተባለ፡፡
ስትሮክ በድንገተኛ የደም መቋረጥ ምክኒያት የሚደርስ አካላዊ ምልክት ነው። በድንገት የአንድ ሰው እጅ፣ እግር እና አፍ መያዝን ወይም የእንቅስቃሴ መገደብን የሚገልጽ ቃል ነው ፡፡ በኢትዮጵያ ስትሮክ ፋውንዴሽን የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶ/ር እስከዳር ከበደ ስትሮክ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የጤና ስጋት መሆኑን ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።ቀደም ባሉት ጊዜያት ምንም አይነት መረጃዎች ባለመኖራቸው ይህ በሽታ የሚታወቅ አልነበረም ፡፡ በቅርቡ በወጡ መረጃዎች መሰረት ስትሮክ ከሦስት እስከ አምስት ባለው የመጀመሪያዎቹ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለ በመሆኑ ትኩረት እንደሚሻ ጠቁመዋል። በስትሮክ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ፋውንዴሽኑ ትምህርታዊ ዝግጅቶችን እንደሚያከናውን የገለፀ ሲሆን ከዚህም ጎን ለጎን አጠቃላይ ምርመራዎችን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሷል። ፋውንዴሽኑ አክሎም ግንዛቤው በስፋት እንዲደርስ ሲምፖዚየም በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ የህክምና ባለሙያዎችን በማምጣት እዚህ ካሉ ሀኪሞች ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ የተለያዪ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብሏል። ይህም አለም የደረሰበትን የስትሮክ ህክምናን የሚመጥን አገልግሎት በሀገር ውስጥ ለመስጠት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል።