በቤት ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ሲያሳድግ የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ
በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ሲያሳድግ የተገኘ ግለሰብ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል። ድርጊቱ የተፈፀመው በክፍለ ከተማው ወረዳ 5 «5 ሺህ ቤቶች» ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ ተጠርጣሪው ናሆም አይናለም የተባለ ግለሰብ መሆኑ ተገልጿል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ መምሪያ ኃላፊ ም/ኮማንደር መርዕድ ደበሌ እንደገለጹት፤ የወንጀል ድርጊቱ ሊጋለጥ የቻለው ከህብረተሰቡ ለፖሊስ በደረሰ ጥቆማ መነሻነት በተደረገ ክትትል ነው። ፖሊስ ጥቆማውን መነሻ በማድረግ ባካሄደው ፍተሻ፣ የጓሮ አትክልት አስመስሎ በ16 ማዳበሪያዎች ውስጥ ተተክሎ ሲያድግ የነበረ «ካናቢስ» የተባለ አደንዛዥ ዕፅ መያዝ ተችሏል። በተጨማሪም ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ ማረፊያ ቤት ሲገባ በተደረገበት የአካል ፍተሻ፣ ተጨማሪ አደንዛዥ ዕፅ በካልሲው ውስጥ ደብቆ ለማስገባት ሲሞክር እጅ ከፍንጅ መያዙ ተገልጿል።