በ2019 የተጠናከረ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚኖር ይጠበቃል - ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስምንተኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡ በዚሁ ወቅት ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳነሱት÷ በሲሚንቶ ምርት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትና በብረታብረት ምርቶች ላይ የታዩ መሻሻሎች በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ንቁ እንቅስቃሴ እንደሚኖረው ይጠቁማሉ፡፡ የአገልግሎት ዘርፍ ዋና ዋና አመላካቾች ማለትም የቱሪስት ፍሰት፣ የአየር ትራንስፖርት፣ የብድር አቅርቦት መሻሻሎች ዘርፉ የበለጠ እንደሚያድግ ማሳያ እንደሆኑ ገልጸዋል። እንዲሁም የወርቅ ወጪ ንግድ፣ የካፒታልና የጥሬ እቃ ምርቶች ገቢ ንግድ እድገቱን እንደሚያጠናክሩም አብራርተዋል። መሰረታዊ ገንዘብ በመስከረም ወር 2019 መጨረሻ 87 ነጥብ 2 በመቶ ዓመታዊ እድገትን እንዳስመዘገበ በማንሳት፤ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው 72 ነጥብ 6 በመቶ አንጻር ጭማሪ እንዳሳየ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላላ የገንዘብ አቅርቦት ዓመታዊ እድገት ባለፈው ዓመት ከነበረው 33 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ላይ 40 ነጥብ 2 በመቶ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህም ከሚጠበቀው የሀገር ውስጥ ምርት አንጻር ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የባንኮች የሩብ ዓመቱ የተቀማጭ ገንዘብ ክምችት 85 ነጥብ 4 በመቶ፤ አጠቃላይ የብድር ክምችት ደግሞ 4 ነጥብ 6 በመቶ ዓመታዊ እድገት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡ የበጀት ፖሊሲ ስርዓት ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ከብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ እንዲሁም ከአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አጀንዳ ጋር የተናበበ እንደነበር አመልክተዋል።