← All news
News Nov 2, 2026 · 5d ago

ሪፓርተር ታገደ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የሪፖርተር ጋዜጣ እና ኦንላይን ስርጭት የምዝገባ ምስክር ወረቀትን ላልተወሰነ ጊዜ አገደ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር ኃ.የተ.የግል ማህበር ሥር የሚታተሙትን ሪፖርተር (አማርኛ)፣ ዘ ሪፖርተር (እንግሊዝኛ) ጋዜጦች እና የኢትዮጵያን ሪፖርተር ዲጂታል ፕላትፎርም የምዝገባ ምስክር ወረቀት ከሰኞ፣ ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ከህትመትና ከስርጭት ሙሉ በሙሉ ማገዱን አስታወቀ። ባለስልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት ላለፈው አንድ ዓመት ባደረገው የይዘት ክትትል፣ በሚዲያ ተቋሙ ተደጋጋሚ የህግ እና የሙያ ስነ-ምግባር ጥሰቶች መፈጸማቸውን ባደረገው ማረጋገጫ ውሳኔው መተላለፉን ገልጿል። እንደ ባለስልጣኑ መግለጫ፣ በጥሰት ከተለዩት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፡- ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጻረሩ ይዘቶችን በተደጋጋሚ ማሰራጨት፣ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ከአርዕስት (Headline) ጀምሮ ማጮህ (Sensationalize ማድረግ)፣ ሀገራዊ መረጃዎችን ከአጠቃላይ አውዳቸው ውጪ በቁንጽል እይታ በመዘገብ በህብረተሰቡ ዘንድ ብዥታና ጥርጣሬ መፍጠር፣ በውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ዲፕሎማሲ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት፣ የሀገር ገጽታንና ብሔራዊ ደህንነትን የሚጎዱ፣ እንዲሁም የህዝቦችን አብሮነት የሚያጠፉ ዘገባዎችን ማቅረብ፣ ሚዛናዊነት የጎደላቸውና በግል ፍላጎት ላይ ተመስርተው የተቋማትን ስም የሚያጠልሹ ዘገባዎችን ማሰራጨት ይገኙበታል። ባለስልጣኑ አክሎ እንዳመለከተው፣ ላለፈው አንድ ዓመት ከተቋሙ ባለቤትና ዋና አዘጋጆች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ለማረም ቢሞከርም ምንም ዓይነት መሻሻል አልታየም። በዚሁ መሰረት፣ ተቋሙ ህጋዊና ሙያዊ ግዴታዎቹን አሟልቶ እስኪያቀርብ ድረስ የምዝገባ ምስክር ወረቀቱ ታግዶ እንደሚቆይና ውሳኔው ከጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በጥብቅ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።