በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር ስጋት አሳሳቢ መሆኑ ተገለጸ
በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋና በርካታ ሴቶችን ለህልፈተ-ህይወት እየዳረገ መምጣቱን ተገልጿል። በሽታው በሀገሪቱ የጤና ዘርፍ ውስጥ አፋጣኝ ትኩረትና ግንዛቤ ማስጨበጫ እርምጃዎችን የሚሻ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉ ተነግሯል። ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የጠቅላላ ቀዶ ጥገና ሀኪም የሆኑት ዶክተር ህይወት ታደሰ እንደገለጹት፤ የጡት ካንሰር በአሁኑ ወቅት በርካታ ሴቶችን እያጠቃ ያለ አደገኛ ህመም መሆኑን ገልፀዋል። በሽታው እንደ ማንኛውም የካንሰር አይነት ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ አንድ ወጥ መነሻ ምክንያት ባይኖረውም፣ የመከሰት እድሉን በእጅጉ የሚጨምሩ የተለያዩ አጋላጭ ሁኔታዎች መኖራቸውን አስረድተዋል። በተለይም ዕድሜያቸው ከ35 እና ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ለበሽታው የመጋለጥ እድላቸው እየጨመረ እንደሚሄድ ተብራርቷል። ቀደም ሲል ለሌሎች ህመሞች ማለትም ለደም ካንሰር ወይም ለሊምፎማ ህክምና በደረት አካባቢ የተወሰደ የጨረር ህክምናም ለጡት ካንሰር ተጋላጭነትን እንደሚያሰፋ ተገልጿል።