አራት ኪሎ ግራም ጫት የሰረቀው ግለሰብ አራት አመት ከአስራ አንድ ወር እስራት ተፈረደበት።
በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ኮቦልቻ ወረዳ ውስጥ አራት ኪሎ ግራም ጫት የሰረቀው የግለሠብ አራት አመት ከአስራ አንድ ወራት እስራት እንደተፈረደበት የምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ፖሊስ ዋና መምርያ አስታውቋል። የፖሊስ ዋና መምሪያው የኮምንኬሽን እና ሚዲያ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ካሲዬ አበበ ለብስራት እንደተናገሩት ተከሳሽ ከድር መሐመድ ኡመር የተባለው ግለሰብ በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ኮቦልቻ ወረዳ ሐቢሶ ቀበሌ ውስጥ የአንዱ ዋጋ አስር ሺሕ ብር የሚያወጣ ጐሲፕ የተባለ እጅግ ውድ ጫት የሰው ግቢ በአጥር ዘሎ በመግባት አራት ኪሎ ሰርቆ ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ሊውል ችልዋል። ተከሳሹ ግምቱ አርባ ሺሕ ብር የሚያወጣ ጫት ቆርጦ በአጥር ዘሎ ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ስር ውሎ የምርመራ መዝገቡ ተጣርቶ በመጠናቀቅ ለአቃቢ እንደተላከ ገልፀዋል። አቃቢ ሕግም ከፖሊስ የቀረበውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ በስርቆት ወንጀል፣ ክስ የመሠረተ ሲሆን ክሱን የተመለከተው የኮቦልቻ ወረዳ ፍርድ ቤት ጥቅምት 20ቀን 2019 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ከድር መሐመድ አራት ኪሎ ግራም ጫት በመስረቁ በአራት አመት ከአስራ አንድ ወራት እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን ኢንስፔክተር ካሲዬ አበበ ጨምረው ገልፀዋል።ዳጉ