አስደንጋጭ‼
የሳይበር ጥቃት ወይስ አስከፊ የተፈጥሮ አደጋ ? ወይስ የተለመደ የአደጋ ዝግጁነት ? ብሪታንያ ፣ ጃፓን እንዲሁም በርካታ የአውሮፓ አገራት መንግሥታት ዜጎቻቸው በድንገተኛ አደጋ ጊዜ ቢያንስ ለ72 ሰዓታት፣ አንዳንዶቹም እስከ አንድ ሳምንት የሚበቃ ምግብ፣ ውሃ፣ የመጀመሪያ እርዳታ መሣሪያዎች፣ ባትሪ፣ ፓወር ባንክና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በቤታቸው እንዲያዘጋጁ እያሳሰቡ ነው። ማሳሰቢያዎቹ እንደ ጦርነት ፣ ሳይበር ጥቃትና የተፈጥሮ አደጋ ባሉ ሁኔታዎች የመብራት፣ የውሃና የመገናኛ አገልግሎቶች ሊቋረጡ እንደሚችሉ በመገመት እርዳታ እስኪደርስ ድረስ ቤተሰቦች ራሳቸውን እንዲችሉ ለማዘጋጀት የቀረቡ ናቸው። ሆኖም እነዚህ የዝግጁነት ጥሪዎች በቅርቡ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት (WW3) ወይም ሌላ አስከፊ የዓለም አደጋ ይከሰታል የሚል ይፋዊ ማስጠንቀቂያ አይደሉም። በብዙ አገራት የ72 ሰዓት ዝግጁነት ምክር የቆየ አሠራር ሲሆን የቅርብ ጊዜዎቹ ጥሪዎችም ነባር የዝግጁነት ማሳሰቢያዎችን የማደስና የማጠናከር እርምጃዎች ናቸው። በሌላ በኩል ፤ የአሜሪካው መከላከያ መስሪያ ቤት ዋና ዋና የጦር ሰፈሮች ያለ ውጭ ድጋፍ ለ90 ቀናት ያህል አስፈላጊ አገልግሎቶቻቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችል ዕቅድ እያዘጋጀ መሆኑን ፎክስ ኒውስ ዘግቧል። ዕቅዱ የሲቪል ሕዝብን ሳይሆን የወታደራዊ ተቋማትን የዝግጁነት አቅም ለማጠናከር የታቀደ ነው።