አሜሪካ በአርሲ በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን ግድያ አወገዘች
በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በንጹሃን ዜጎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የታለሙ የግድያ ወንጀሎች ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠሩበት የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው በሰጠው መግለጫ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር ወይም በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጸሙ ማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች ፈጽሞ ተቀባይነት የሌላቸውና ወዲያውኑ ሊቆሙ የሚገባቸው አስነዋሪ ድርጊቶች መሆናቸውን ገልጿል። የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ አያይዞም፣ የተከሰተውን አሳዛኝ ሁኔታ ለመረዳት ጥረቶች እየተደረጉ ባለበት በዚህ ሰዓት፣ ማህበረሰቡን የበለጠ ሊያለያዩና ክፍፍል ሊፈጥሩ ከሚችሉ ነገሮች መቆጠብ እንደሚገባ አሳስቧል። በዜጎች ላይ የሚደርሱ እንዲህ ያሉ አስከፊ ጥቃቶች ዘግናኝ መሆናቸውን ጠቁሞ፣ በጉዳዩ ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማውም አስታውቋል። በመጨረሻም የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ የኢትዮጵያ መንግሥት አፋጣኝ ማጣራት በማካሄድ፣ ወንጀሉን የፈጸሙ አካላትን ለሕግ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርቧል። የሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እና ጥፋተኞች ተጠያቂ እንዲሆኑም አጽንኦት ሰጥቷል።