«በወልቂጤ ዙሪያ በደረሰ ጥቃት አርቲስት አንተነህ ተኸርቁና ሌሎች አሽከርካሪዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ»
አርቲስት አንተነህ ተኸርቁ የዕለት ከዕለት ሥራውን ለማከናወን በነበረበት የኮሮላ ተሽከርካሪ ከጅማ የመጣች ደንበኛን ይዞ ከአዲስ አበባ ወደ ሰባት ቤት ጉራጌ (ወልቂጤ) በመጓዝ ላይ በነበረበት ወቅት ጥቃቱ ሰለባ ሆኗል። በጉዞ ላይ እያለ ምሽት 4:30 አካባቢ የተሽከርካሪው ጎማ በመበላሸቱ የተሽከርካሪውን ጎማ ለመቀየር ወይም ለመጠገን ባቆመበት አቅራቢያ በነበሩ የታጠቁ አካላት ጥቃት እንደተፈጸመበት ተመላክቷል። በትላንትናው ዕለት በተፈጸመው በዚህ አሳዛኝ ድርጊት አርቲስቱን ጨምሮ ሌሎች አሽከርካሪዎች ሕይወት ማለፉ የተገለጸ ሲሆን፣ በጉዞ ላይ ባሉ ንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ መሰል ጥቃቶችን ለማስቆም የጸጥታ መዋቅሮች የመንገድ ላይ ደህንነትንና ቁጥጥርን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ማኅበረሰቡ ጥሪ ማቅረቡ ታውቋል። ለሟቾች ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና ለአድናቂዎቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።