በትግራይ ክልል በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች ተገደሉ
በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ዛሬ አርብ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች መገደላቸውን የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) ዘገባ አመላከተ። ዜና ወኪሉ የህክምና ምንጮችን እና የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው በጥቃቱ በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሶል። አንድ የዓይን እማኝ ለዜና ወኪሉ በሰጡት ቃል፤ ጥቃቱ የተፈጸመው ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ ተመቶ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ የነበረ እህልን በማንሳት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ መሆኑን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ግጭቶችን የሚከታተለው ኤሲኤልኢዲ (ACLED) የተሰኘው ተቋም ባወጣው መረጃ፤ ጥቃቱ በራማ ከተማ ሰላማዊ ሰዎችን በያዘ የ«አይሱዙ» ተሽከርካሪ ላይ የተፈጸመ መሆኑን ጠቁሟል። በጥቃቱ 12 ሰላማዊ ሰዎች ከመገደላቸው በተጨማሪ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች መጎዳታቸውን እና በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን አስታውቋል። ተቋሙ አክሎ እንዳመለከተው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አጋሩ የትግራይ የሰላም ሀይል በማዕከላዊ ትግራይ ዞን ተንቤን የተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው በዚያም የድሮን ቅኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።