በእርግዝና ወቅት በቀን ከሁለት ስኒ ቡና በላይ መጠጣት የፅንስ ማቋረጥን ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቆመ
በእርግዝና ወቅት ሙሉ ለሙሉ ቡና መጠጣት ባይከለከልም ከመጠን ያለፈ ሲሆን ግን በእናትየዉም ይሁን በህፃኑ ላይ የተለያዩ ችግሮችን እንደሚያስከትል ጥናቶች አመልክተዋል። የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ታዘባቸዉ ዉዴ ከብስራት ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት ከሆነ እንደየስኒው መጠን እና የቡናዉ ዉፍረት በዉስጡ የሚይዘዉ ካፊን የሚለያይ በመሆኑ ነፍሰጡር ሴቶች በቀን ከሁለት ስኒ ቡና በላይ ባይጠጡ ይመከራል ። በእርግዝና ወቅት በቀን ዉስጥ ከፍተኛ መጠን ያለዉ ቡና መጠጣት በተለይም የመጀመሪያዎቹ ሶስት እና አራት ወራት ላይ የማቅለሽለሽ ወይንም የሆድ ህመምን ሊያባብስ እንደሚችል ተገልጿል። በእናትየዉ ላይ ከሚያሳድረዉ የጭንቀት ፣ የእረፍት ማጣት እና የእንቅልፍ ችግር በተጨማሪ የህፃኑን እድገትም እንደሚጎዳ ተጠቁሟል ። ቡና ዉስጥ ያለዉ ካፊን በማህፀን በኩል ወደ ፅንሱ የሚተላለፍ ሲሆን በእርግዝና ወቅትም ከፍተኛ መጠን ያለዉ ቡና መጠጣት የፅንስ ማቋረጥን ሊያስከትል እንደሚችል ጥናቶች እንደሚያሳዩ ስፔሻሊስቱ ገልፀዉልናል።