በ7 ዓመቱ ህፃን ላይ ግድያ የፈጸመው ተጠርጣሪ ለማምለጥ ሲሞክር በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ አለፈ‼️
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የ7 ዓመት ህፃንን አግቶ በመግደል 4 ሚሊየን ብር ሲጠይቅ የነበረው የጥበቃ ሠራተኛ፣ ፍለጋ በ ተከናወነበት ወቅት ከፖሊስ አባላት ጋር ግብግብ ፈጥሮ ለማምለጥ ሲሞክር በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ። እንደ ፖሊስ መረጃ፣ ጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ.ም. በግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት በጥበቃ ሠራተኝነት ተቀጥሮ ይሠራ የነበረው ግሩም ወርቁ የተባለ ተጠርጣሪ ህፃኑን "ሳር አጭደን እንመለሳለን" በማለት ወደ ቀርሳ ቅዱስ ሚካኤል ጫካ ወስዶታል። በቦታውም ህፃኑን በእጁ ገመድ ያስያዘበትን ፎቶ ካነሳ በኋላ በገመድ አንቆ በመግደል አካሉን በደረቅ ፅድ አልብሶ ከአካባቢው ተሰውሯል። ተጠርጣሪው ህፃኑን ከገደለ በኋላም በህይወት ያለ አስመስሎ ፎቶዎቹን ለቤተሰቡ በመላክ ገንዘብ ሲጠይቅ እንደነበር በምርመራ ተረጋግጧል። ፖሊስ በሁለት ቡድኖች ከፍሎ ባደረገው ክትትል፣ ጥቅምት 15 ቀን 2019 ዓ.ም. ተጠርጣሪውን በአፋር ክልል ገቢረሱ ዞን አርጎባ ልዩ ወረዳ ጋቸኒ ከተማ በቁጥጥር ሥር ማዋል ችሏል። ተጠርጣሪው ከተያዘ በኋላ በሰጠው ቃል መሠረት ፎቶ ያነሳሁት ልጁን ይዤ በምንቀሳቀስበት ወቅት ልያዝ ስለምችል በህይወት ያለ በማስመሰል ገንዘብ ለመቀበል በማሰብ ነው ሲልም ቃሉን ሰጥቷል፡፡ በተደረገው ፍለጋም የወንጀሉ መሣሪያ የነበረው ገመድ፣ የህፃኑ አልባሳት እና በአውሬ የተበሉ የተበጣጠሱ የሰውነት አካላት ተገኝተዋል። በመቀጠልም የህፃኑ የራስ ቅል ይገኛል በተባለበት ስፍራ ተጨማሪ ፍለጋ ለማድረግ ተጠርጣሪውን ይዞ ወደ ቦታው በተኬደበት ወቅት፣ ግለሰቡ ከፖሊስ ጋር ግብግብ በመፍጠር ገደል ለገደል ለማምለጥ ሞክሯል። በዚህም ወቅት በተወሰደበት የእርምጃ ጥይት ቆስሎ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል። ፖሊስ ሕብረተሰቡ የቤት ሠራተኛም ሆነ ጥበቃ ሲቀጥር ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና ህፃናት ተገቢውን ክትትል የሚሹ በመሆናቸው የሚደረገውን ክትትል እንዲያጠናክር አሳስቧል።