የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ዙሪያ
አዲስ የጉዞ ገደብ እና ማሳሰቢያ አወጣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ዙሪያ አዲስ የደህንነት ማስጠንቀቅያ ያወጣ ሲሆን፤ ዜጎቹ ወደ አገሪቱ ከማድረግ ጉዞ እንዲቆጠቡ አሳስቧል። ኤምባሲው በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሞያሌ አካባቢዎች የሚታዩ የጸጥታ ሁኔታዎችን በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን ገልጾ፣ በአክሱም እና በሽሬ አውሮፕላን ማረፊያዎች የበረራ አገልግሎቶች አሁንም ተቋርጠው በመገኘታቸው ዜጎች ስለ በረራ መረጃ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ መክሯል። በመግለጫውም የአሜሪካ ዜጎች ወደ አማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች (በተለይ ሰሜን አፋር) ከቶውንም እንዳይጓዙ አበክሮ የጠየቀ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ሁኔታዎች አመች በሚሆኑበት ጊዜ ፈጥነው አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል። የጸጥታ ሁኔታ በማንኛውም ጊዜ ሊለወጥ እንደሚችል በመጥቀስም ጉዞዎችን ዳግም እንዲያስቡበት አጥብቆ አሳስቧል።