የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ "የመደመር"
መጽሐፍ በሩሲያኛ ተተርጉሞ ተመረቀ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ "የመደመር" መጽሐፋቸው ወደ ሩሲያኛ ተተርጉሞ መመረቁንና በምረቃውም ላይ በአካል በመገኘታቸው ትልቅ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው ገለጹ። መጽሐፉ ከዚህ ቀደም በእንግሊዝኛ፣ በቻይንኛ እና በአረብኛ መታተሙ ይታወሳል፤ አሁን ደግሞ በሩሲያኛ መዘጋጀቱ የኢትዮጵያ ሐሳብና ፍልስፍና ድንበር ተሻግሮ ለብዙኃን እንዲደርስ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። ሩሲያ ለብዙ ኢትዮጵያውያን የትምህርት ቦታ እንደነበረች ሁሉ፣ አሁን የኢትዮጵያ ሐሳብ ለሩሲያ አንባቢያን መድረሱ የዕውቀት ልውውጡን ሙሉ እንደሚያደርገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በተጨማሪም መጽሐፉ እንዲዘጋጅና እንዲተረጎም ከፍተኛ ጥረት ላደረጉት የሩሲያ ቱዴይ (RT) ባለሙያዎችና አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ይህ እርምጃ የኢትዮጵያን ባህልና እውቀት ለዓለም ለማስተዋወቅ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ጠንካራ የሐሳብ ድልድይ ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል።