የአፍላ ቶክሲን መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ የለውዝ ቅቤ ምርቶችን መጠቀም ለካንሰር ህመም ተጋላጭ ያደርጋሉ ተባለ
👉የፕላምፕኔት ምርትንም አስፈላጊ ባልሆነ ሰዓት መጠቀም በጉበት ላይ ጉዳትን እንደሚያስከትል ተገልጿል። ህሊና ኢንሪች ፉድስ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በሕፃናት ፣በነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶች ላይ የሚከሰትን የሥነ-ምግብ፣ የቪታሚን እና ሚኒራል እጥረትን ለመቅረፍ ልዩ አልሚና የሕክምና ምግቦችን እያመረተ እንደሚገኝ አስታውቋል። ለምግብ እጥረት ተብለው የሚመረቱ ምርቶችን ለውጪ ገበያ ማቅረብም ሆነ መሸጥ የተከለከለ እና በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን ለብስራት ሬዲዮ የተናገሩት በህሊና ኢንሪችድ ፉድስ የጥራት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ የሆኑት ውብአንተ ክብረት ናቸው።የፕላምፕኔት አና ፕላምፕሰፕ ምርቶችን ለማንኛውም ጤነኛ ሰው መሰጠት የማይችል እና ለጤና የማይመከር መሆኑን ገልፀው በጉበት እንዲሁም በሌሎች የሠውነት ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል አስገንዝበዋል። ምርቱ ከፍተኛ የሆነ ፋትን በውስጡ ስለያዘ በመቀንጨር ለተጠቁ ህጻናት ብቻ መሰጠት ይኖርበታል ብለዋል።ይህ ምርት በመቀንጨር የተጠቁ ህጻናት ምርቱን መጠቀም ከጀመሩ ከስምንት ቀናት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ለውጥ ማምጣት የሚያስችላቸው እንደሆነ በተቋሙ የለውዝ ቅቤ እና የለውዝ ምርት ሃላፊ አቶ ጌታሁን ጫላ ነግረውናል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ ፎርቲፋይድ የሆነ እና ከአፍላ ቶክሲን የጸዳ በቀን 80 ቶን የለውዝ ቅቤ እያመረተ ይገኛል :: አቶ ጌታሁን አክለውም አፍላ ቶክሲን ያላቸውን ምርቶች መጠቀም በጊዜ ብዛት ለካንሰር ህመም ተጋላጭ ያደርጋሉ ሲሉ ተናግረዋል። እንዲሁም መጠናቸው ያልተረጋገጠ እና ጥራታቸውን ጠብቀው ያልተመረቱ ምርቶችን መጠቀም በካንሰር ህመም ከመጠቃት ባለፈ እስከ ሞት የሚያደርስ መሆኑ ተጠቁሟል።በመሆኑም ማህበረሰቡ በተለይም እንደ ለውዝ ቅቤ ያሉ ምርቶችን ሲጠቀም ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ሀላፊው አሳስበዋል።