ሚዳቆን በጦር ገድለው ስጋውን ሲመገቡ የነበሩ 3 ግለሰቦች ተያዙ
በደቡብ አሪ ወረዳ ሚዳቆን በጦር በመግደል ስጋውን ለግል ጥቅም ሲያውሉ ተገኝተዋል የተባሉ ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። ግለሰቦቹ በደቡብ አሪ ወረዳ ባላምር ቀበሌ ዋልሻአት/ታማ ፓርክ በተባለ አካባቢ የንብ ቀፎ ለመስቀል በሚል በመገኘት ሚዳቆን በጦር ከገደሉ በኋላ ሥጋውን ሲመገቡ መያዛቸውን የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ጋንሣ ብርሃኑ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል። ተጠርጣሪዎቹ ከተያዘው ማስረጃ ጋር በቶልታ ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር በመዋል በድርጊቱ ላይ የምርመራ ሂደት እየተካሄደ መሆኑን ተገልጿል። ህገወጥ የዱር እንስሳት አደን በህግ የተከለከለና ቅጣት የሚያስከትል በመሆኑ ማህበረሰቡ የዱር እንስሳትን ከህገወጥ አደን ለመጠበቅ መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል። በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚካሄደው ምርመራ ተጠናቆ የፍርድ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግ ኢንስፔክተር ጋንሣ ብርሃኑ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።