← All news
News Oct 27, 2026 · 11d ago

የታሸጉ ውኃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የጋራ መግባባት ተደረሰ

በመዲናችን አዲስ አበባ የታሸጉ ውኃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ ለማቅረብ የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል። ቢሮው ከውኃ አምራቾች ማኅበር አመራሮች ጋር ባካሄደው የምክክር መድረክ፣ በታሸጉ ውኃዎች አቅርቦት፣ የዋጋ ጭማሪና ጥራት ዙሪያ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ እንደገለጹት፤ የምክክሩ ዋና ዓላማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታሸጉ ውኃዎች ላይ የታየውን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ መንስኤ ከአምራቾቹ አንደበት በመስማት ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫ ለመቀየስ ነው። በሌላ በኩል የማኅበሩ አመራሮች በምርትና በግብይት ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ያነሱ ሲሆን፣ በተለይም በማምረቻ ጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ላይ የሚታየው የደላሎች ጣልቃ ገብነት እልባት እንዲያገኝ ጠይቀዋል። በውይይቱ ማጠቃለያም አምራች ፋብሪካዎች የታሸገ ውኃን ለአከፋፋዮችና ለቸርቻሪዎች የሚሸጡበትን የተመጣጣኝ ዋጋ መጠን በየግላቸው በመወሰን፣ በማኅበራቸው አማካይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለንግድ ቢሮው ለማሳወቅ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።