← All news
News Oct 27, 2026 · 12d ago

የሚያጣብቁ የውስጥ ሱሪዎችን የሚያዘወትሩ እና ላፕቶፕን እግራቸዉ ላይ አድርገዉ የሚጠቀሙ ወንዶች ለመካንነት ተጋላጭ ናቸው ተባለ፡፡

መካንነት አብዛኛዉን ጊዜ ሴቶች ላይ ያለ ችግር ተደርጎ ቢወሰድም ከጠቅላላው የመካንነት ችግር እስከ 18 በመቶ የሚሆነዉን ድርሻ የሚይዙት ወንዶች መሆናቸዉን ጥናቶች ያሳያሉ ። ሁለት ጥንዶች ምንም አይነት የእርግዝና መከላከያ ሳይጠቀሙ ከአንድ ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ዉስጥ እርግዝና ካልተፈጠረ የመካንነት ችግር ተብሎ የሚገልፅ ሲሆን የወንዶች መካንነት በዋናነት ከዘር ፍሬ ምርት ብዛት ፣ጥራት እና እንቅስቃሴ ሂደት ጋር የተያያዘ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይገልፃሉ ። ከብስራት ሬዲዮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ጠቅላላ ሀኪም ዶክተር ዙቤይዳ ሁሴን እንደገለፁት ከሆነ የወንድ የዘር ፍሬ ጤናማ እና ጥራት ያለዉ ሰፐርም ማምረት የሚችለዉ ከሰዉነት መደበኛ ሙቀት በቀዘቀዘ አከባቢ ነዉ ። ላፕቶፕ እግር ወይም ጭን ላይ ሲቀመጥ የወንድ ዘር ፍሬ መደበኛ ሙቀትን ይጨምራል ። ይህም የሰፐርም ብዛትን ፣የመንቀሳቀስ ብቃትን እና ቅርፅን ስለሚጎዳ የወንዶችን የመዉለድ አቅምን በመቀነስ ለመካንነት ሊያጋልጣቸዉ እንደሚችል ነዉ ዶክተር ዙቤይዳ የሚገልፁት ። በመሆኑም ላፕቶፕን ሁልጊዜም በጠረጴዛ ወይም በሌላ ጠፍጣፋ ነገር ላይ አስቀምጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል ። የሆርሞን መዛባት ፣በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች ፣ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት ፣ሲጋራ ማጨስ ፣ከመጠን ያለፈ ዉፍረት እንዲሁም የሚያጣብቁ የዉስጥ ሱሪዎችን ማድረግ ወንዶችን ለመካንነት ከሚያጋልጡ ሌሎች ምክኒያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸዉ ተብሏል ።