“የአንድ መጠነኛ ሀገር የመከላከያ ትጥቅ
ሊሆን የሚችል የጦር መሳሪያ ተቆጣጥረናል” መከላከያ ሰራዊት በምጽዋ ወደብ የተላለፈ፣ “የአንድ መጠነኛ ሀገር የመከላከያ ትጥቅ ሊሆን የሚችል የጦር መሳሪያ መቆጣጠሩን” የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ተናገሩ። ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰራዊቱ በአባይ ውሃ እና በቀይ ባህር የሚገኘውን የኢትዮጵያ ጥቅም “ከማስከበር ውጪ አማራጭ የለውም” ብለዋል። ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ይህንን ያሉት፤ ዛሬ እሁድ ጥቅምት 15፤ 2019 በተከበረው የመከላከያ ሰራዊት የምስረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። የመከላከያ ሰራዊት ምስረታ በዚህ ዕለት እንዲከበር የተደረገው፤ አጼ ምኒልክ የጦር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያቋቋሙበት እና ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን የጦር ሚኒስትር አድርገው የሾሙበት ዕለት በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል። በዚህ መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ 12 ደቂቃ ገደማ የፈጀ ንግግር ያደረጉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ቅድሚያ ሰጥተው ያነሱት ጉዳይ ባለፈው መስከረም አጋማሽ ወር በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ውጊያ ነው። በሰሜን ወሎ፣ በዋግ እና በአፋር ግንባሮች የተካሄደውን ውጊያ “ጦርነት” ሲሉ የጠሩት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፤ ጦርነቱን “የከፈተው” ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሆኑን ተናግረዋል። ህወሓትን “በመላክ” ጦርነት እንዲከፍት ያደረጉት፤ “ከግብጽ እስከ ካርቱም እና አስመራ የተቀናጀው ጽምጾ ነው” ሲሉ ወንጅለዋል። ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ጠላቶቻችን” ሲሉ የጠሯቸው ሀገራት፤ ለህወሓት በኤርትራ በሚገኘው የምጽዋ ወደብ በኩል የጦር መሳሪያ “አስተላልፈዋል” ሲሉም ከስሰዋል።