«የታሪክ ጠላቶቻችን እርኩስ መንፈስ ተመቷል”- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የሀገሪቱን ሰላምና ሉዓላዊነት ለማፍረስ የተነሱ አካላት ሙከራ እንደከሸፈ ገለጹ። የመከላከያ ሠራዊቱን ለማፍረስ የተንቀሳቀሱ የታሪክ ጠላቶች እርኩስ መንፈስ በእግዚአብሔር ውሳኔ መመታቱንም ተናገሩ። ፊልድ ማርሻሉ በንግግራቸው፣ ኢትዮጵያን በሁለት ሳምንት ውስጥ ለመቅበር አቅዶ የነበረው ኃይል ጊዜው ሳይሞላ መቀበሩን አስታውሰዋል። በተጨማሪም ትግራይ አዳዲስ ሐሳቦችን፣ ፓርቲዎችንና አሠራሮችን እንዲሁም ሰላምና ልማትን እንደምትፈልግ ገልጸዋል። ለግማሽ ምዕተ ዓመት የቆየው የትግል መስመር የትግራይን ሕዝብ እንደጎዳውም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድማዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ድጋፍ እንዲያደርግ ያሳሰቡት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ «አንድ የራሱ ጣት ታሞበት ዝም የሚል ሰብዓዊ ፍጡር የለም» በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል።