ከናይሮቢ የሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ አንድ ሰው በሕይወት ተረፈ፤ የ31 ሰዎች ደብዛ አሁንም አልተገኘም
በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ፣ ኢስትሊ (Eastleigh) አካባቢ በተደረመሰው ባለ 18 ፎቅ ሕንፃ ፍርስራሽ ውስጥ ተቀብሮ የነበረ አንድ ሰው በነፍስ አድን ሠራተኞች አማካኝነት በሕይወት መውጣቱን ስፑትኒክ ዘግቧል። ግለሰቡ ከፍርስራሹ ከወጣ በኋላ ወደ ኬንያ ብሔራዊ ሆስፒታል ተወስዶ የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል። ከሕንፃው መደርመስ በኋላ የጠፉ ሰዎችን የመፈለግ ሥራ ቀጥሏል። እስካሁን የ31 ሰዎች ደብዛ አልተገኘም። ከዚህ ቀደም ጠፍተዋል ተብለው ከተመዘገቡት መካከል ሁለት ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሰላም መገናኘታቸው ተረጋግጧል። የአደጋ ጊዜ ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ ሕንፃው ከመደርመሱ በፊት አንዳንድ ሠራተኞች ከሥፍራው ወጥተው ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የጠፉ ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ማጣራት እየተካሄደ ነው። በተያያዘም፣ የኬንያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአደጋው ለተጎዱና ለተጨነቁ ቤተሰቦች የሥነ-ልቦና ድጋፍና የምክር አገልግሎት ለመስጠት የአደጋ ጊዜ ኦፕሬሽን ማዕከል አቋቁሞ እየሠራ ይገኛል።