← All news
News Oct 24, 2026 · 14d ago

በአለም ባንክ መለኪያ መስፈርት በቀን ከ480 ብር ገደማ በታች የሚያገኝ ሰው አስከፊው የድህነት ወለል ውስጥ ያለ ተብሎ ይመደባል፡፡

በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነቱን ፣ የዋጋ ንረቱን ከግምት ያስገባ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲኖር ተደጋግሞ ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች የደመወዝ ሁኔታ ደግሞ የበለጠ አሳሳቢ መሆኑ ይነገራል፡፡ በቅርቡ ይፋ በሆነ ጥናት እንደተረጋገጠው እነዚህ ሰራተኞች ወር ሙሉ ሰርተው የሚከፈላቸው ደመወዝ በአንድ በደረጃው መለስ ያለ ምግብ ቤት ቁርስ በልቶ ምሣ የሚያስደግም አይደለም ተብሏል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የመንግስት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ የቤት ኪራይ ለመሸፈን ባለመቻሉ ምክንያት በየቢሮ ህንጻዎች ስር፣ በጥበቃ ቤቶች እና ከጥበቃ አባላት ጋር በመነጋገር ድንኳንና ፕላስቲክ ዘርግተው ለማደር መገደዳቸው እየተዘገበ ይገኛል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ለሸማቾች ማህበራት 500ሚ ብር መመደቡን ከቀናት በፊት ገልጿል።