በስድስት ኪሎ አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ፦ የ1 ሰው ሕይወት ሲቀጥፍ በ11 ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት አደረሰ
በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው ስድስት ኪሎ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ጥቅምት 13 ቀን 2019 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡30 ገደማ ከባድ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተከሰተ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ አደጋ ምርመራ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መንግስቱ ታደሰ እንደገለጹት፣ ከመገናኛ ወደ አፍንጮ በር ሲጓዝ የነበረ የከተማ አውቶቡስ ከመስመር ወጥቶ ባደረሰው አደጋ የ40 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ሴት በመግጨት ወዲያው ሕይወታቸው እንዲያልፍ ያደረገ ሲሆን፣ በሌሎች ሁለት እግረኞች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት አድርሷል። ከዚሁ አሳዛኝ የሰው ሕይወትና አካል ጉዳት በተጨማሪ አውቶቡሱ በቦታው ቆመው በነበሩ 11 ተሽከርካሪዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ከፍተኛ የንብረት ውድመት አድርሷል። አሽከርካሪዎች የሰዎችን ሕይወት የመጠበቅ ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያሳሰበው የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ፣ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ተመሳሳይ አደጋዎችን፣ የሕይወት መስዋዕትነትንና የንብረት ውድመትን ለመከላከል በጥናት ላይ የተመሰረተ ሕግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።