የመንጋጋ አጥንት አቀማመጥ ችግርን ማስተካከል የሚያስችል ቀዶ ህክምና እየሰጠ መሆኑን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አስታወቀ
👉ህክምናው ከተጀመረ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሶስት ሰዎች ቀዶ ህክምና ተደርጎላቸዋል ። የህክምናው ዓላማ የፊት ገጽታን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን የመንጋጋን ተግባር በማሻሻል ምግብን በትክክል ማኘክን፣ መናገርንና በአንዳንድ ሁኔታዎች የመተንፈስ ችግሮችን ማሻሻል መሆኑ ተገልጿል። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የጥርስና የመንጋጋ ቀዶ ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና የፊትና መንጋጋ ቀዶ ሕክምና ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አዲስ ካሳሁን ለብስራት ሬዲዪ እንደገለፁት በብሬስ ማስተካከል የማይቻሉ ከመንጋጋ አጥንት አቀማመጥ ጋር የተያያዙ ችግሮች በቀዶ ህክምናው ሊስተካከሉ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል። የመንጋጋ አጥንት ትክክለኛ አቀማመጥ አለመኖር በአካባቢው ባሉ ጡንቻዎች ላይ ውጥረት በመፍጠር ተደጋጋሚ የፊትና የመንጋጋ ሕመም ሊያስከትል እንደሚችልም ባለሙያው አብራርተዋል። በተጨማሪም የታችኛው መንጋጋ ከመጠን በላይ ወደ ኋላ መገፋት የአየር መተላለፊያን በማጥበብ በእንቅልፍ ወቅት የመተንፈስ ችግርን ሊያስከትል ወይም ሊያባብስ እንደሚችል ገልጸዋል።ቀዶ ህክምናው በአፍ ውስጥ የሚከናወን በመሆኑ በፊት ላይ የሚታይ ጠባሳ እንደማይተው ዶክተር አዲስ አስረድተዋል። የመንጋጋ አጥንት አቀማመጥ ችግር የፊት ገጽታን ብቻ ሳይሆን የአፍና የጥርስ ተግባርን ሊጎዳ እንደሚችል ጠቁመው ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ሰዎች ተገቢውን ምርመራና ህክምና ለማግኘት ወደ ጥርስና የመንጋጋ ህክምና ባለሙያዎች እንዲቀርቡ አሳስበዋል።