በአዲስ አበባ የሉኳንዳ ቤቶች የስጋ ዋጋን በኪሎ 500 ብር ቀነሱ
የአዲስ አበባ ሉኳንዳ ቤቶች ማህበር በከተማዋ የስጋ ዋጋን በኪሎ 500 ብር ለመቀነስ መወሰኑን አስታወቀ። በውሳኔው መሠረት ለወጥና ለጥብስ የሚሆን ስጋ በሁሉም ሉኳንዳ ቤቶች በኪሎ 2,500 ብር እስከ ጠዋቱ 4:00 ድረስ ለሸማቾች እንደሚቀርብ ተገልጿል። የማህበሩ አመራሮች ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅና ከከተማዋ የስጋ ቤት ባለቤቶች ጋር ከተወያዩ በኋላ ውሳኔውን ይፋ አድርገዋል። በማህበሩ አመራሮች ገለጻ፣ ከጥቅምት 14 ቀን ጀምሮ የስጋ ቤቶች ከቀድሞው ዋጋ በኪሎ 500 ብር ቀንሰው እንዲሸጡ ተወስኗል። የማህበሩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ወልደማርያም አባተ፣ ከስጋ ተረፈ ምርቶች ጋር በተያያዘ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸው፣ እነዚህ ሥራዎች ሲሳኩ የስጋ ዋጋ የበለጠ ሊቀንስ እንደሚችል ተናግረዋል። ውሳኔው የሸማቾችን ጥያቄና የመግዛት አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት መወሰኑንም አመልክተዋል።በዚህ ጉዳይ አዲስ ሪፖርተር ከዚህ በፊት የስጋ ተጠቃሚዎችን ቅሬታ መዘገቧ የሚታወስ ነው። የንግድ ቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ፣ የዋጋ ቅነሳው በሁሉም ሉኳንዳ ቤቶች በወጥነት ተፈጻሚ መሆኑን የንግድ ቁጥጥር ባለሙያዎች እንዲከታተሉ አሳስበዋል። ውሳኔውን የማይተገብሩ የስጋ ቤቶችን በተመለከተም ሕብረተሰቡ በ 8588 የመረጃ መስጫ ቁጥር ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።