ዕድሜ ጠግቦ የቆየው የቦርከና ድልድይ ፈርሶ በአዲስ ሊገነባ ነው
በወሎ ኮምቦልቻ ከተማ ከ1946 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 63 ዓመታት ሲያገለግል የቆየው የቦርከና ድልድይ በአዲስ ድልድይ ሊተካ ነው። ዕድሜው በመጨመሩና የትራፊክ ፍሰቱን በበቂ ሁኔታ ማስተናገድ ባለመቻሉ አዲሱ ድልድይ እንዲገነባ መወሰኑ ተገልጿል። አዲሱ የቦርከና ድልድይ የእግረኛና የሳይክል መንገድን ጨምሮ 40 ሜትር ስፋት የሚኖረው ሲሆን፣ ለግንባታው 300 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። ሙሉ ወጪውንም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እንደሚሸፍን ታውቋል። ግንባታው በቅርቡ እንደሚጀመር የተገለጸ ሲሆን፣ አዲሱ ድልድይ እስኪጠናቀቅ ድረስ የትራፊክ ፍሰቱን ለማስተናገድ በቀድሞው የመኪና ማዘያ በኩል አድርጎ በመናፈሻው የሚወጣ ተለዋጭ መንገድ እየተሰራ ይገኛል።