አቶ ጌታቸው ረዳ ስለ ትግራይ ውጊያ እና ስለ ኤርትራ ተሳትፎ ምን አሉ?
በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ ሲጀመር ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና ፋኖ በአማራ እና አፋር ክልሎች ጠልቀው በመግባት የጅቡቲን መስመር እንዲቆርጡ በኤርትራ መንግስት “ትዕዛዝ” ተሰጥቷቸው እንደነበር አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። ውጊያው በአፋር ክልል ወደሚገኙ አካባቢዎች ሲዘልቅ “የኤርትራ ኃይል በተወሰነ ደረጃ” በከባድ መሳሪያ “ድጋፍ” እያደረገ፤ ለኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግድ ቁልፍ መተላለፊያ የሆነውን የጅቡቲ አውራ ጎዳና የመቁረጥ ስሌት እንደነበር አቶ ጌታቸው ገልጸዋል። ላለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካሪ ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ ጌታቸው ውጊያውን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ እና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ባዘጋጁት የፖሊሲ የውይይት መድረክ ላይ ነው። “ህብረት ወይስ ክደት? ጸረ-ኢትዮጵያ ጥምረት ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ በትናንትናዉ ዕለት ሐሙስ ጥቅምት 12፤ 2019 የተካሄደውን ውይይት በአብዛኛው የታደሙት፤ የመከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ መኮንኖች ናቸው። መከላከያ ሰራዊት በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ከኤርትራ ድንበር በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ “አዲ ፍታው” የተባለች ቦታ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ግጭት ቢፈጠር “የኤርትራ ምሽግ የመሰበር እድሉ ሰፊ ነው። ምሽጉ ከተሰበረ በኋላ አስመራ ለመግባት የሚወስድ በጣም አጭር ጊዜ ነው” ብለዋል።