← All news
News Oct 22, 2026 · 16d ago

ወረራ አልፈፀምኩም-ኤርትራ‼️

‹‹በኢትዮጵያ ላይ ወረራ እንደፈፀምን የሚገለፀው ክስ ሙሉ በሙሉ የተፈጠረ ውሸት ነው›› ሲል የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ‹‹በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ›› በሚል ዛሬ ዘለግ ያለ መግለጫ አውጥቷል፡፡ በዚህ መግለጫው ‹‹የኤርትራ ሉአላዊ ግዛት ለስምምነት ወይንም ለድርድር አይቀርብም›› ያለ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ‹‹ለስትራቴጂያዊ አላማ አስፈላጊ ነው›› በሚል የኤርትራን ሉአላዊ ድንበር ለመውረርና ለመጣስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ እየተባባሰ ለመጣው አለመረጋጋትና ቀውስ ‹‹በኢትዮጵያ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ሆነ ተብሎ ለአመታት የፈፀመ የጂኦ ፖለቲካ ጥቃት ውጤት ነው›› በማለት ክስ ያቀረበው መግለጫው ይህም በወታደራዊ ዛቻ፣ ዲፕሎማሲያዊ ጠላትነት፣ በኢኮኖሚ ማስፈራሪያና በገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ጨምሮም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ‹‹ሁሉም ወገኖች›› ወይንም ‹‹ሁሉም አካላት›› መረጋጋትን እንዲያሳዩና ውጥረቱን እንዲያረግቡ በሚል የሚቀርበውን ጥሪ ‹‹ህጋዊነት የጎደለውና ለዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጎጂ ነው›› በማለት ገልፆታል፡፡ እንዲህ አይነት መግለጫዎች ሉአላዊነቱን የሚከላከልንንና ጥቃት ፈፃሚውን እኩል የሚያስቀምጡ መሆናቸውን ጠቅሶምነ ለተጨማሪ ሀላፊነት የጎደለው ድርጊት በር እንደሚከፍቱ አሳስቧል፡፡ በማስከተልም ‹‹ኤርትራ ወረራ ፈፅማለች የሚለው ክስ ሙሉ በሙሉ የተፈጠረ ውሸት ነው፡፡ ይህ መሰረት የለሽ ክስ ተጠያቂነትን ለማምለጥ፣ አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማታለልና የተጀመሩ የግዛት ማስፋፋት ምኞቶችን ህጋዊ ለማድረግ የተደራጀ የመረጃ ጦርነት አካል ነው›› ብሏል፡፡