← All news
News Oct 21, 2026 · 17d ago

በአዲስ አበባ ከተማ በመሠረታዊ የዕለት ተዕለት ፍጆታዎችና በቤት ኪራይ ላይ እየታየ ያለውን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ቁልፍ እርምጃዎች እንደሚወሰድ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ

ከንቲባዋ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ሰፊ ውይይት እንደገለጹት፤ የሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ የዳቦ፣ የታሸገ ውኃና የቤት ኪራይ ዋጋዎችን ያካተተ ዝርዝር ግምገማ ተካሂዷል። ይህንን የኑሮ ጫና ከመሠረቱ ለማቃለል ከተማ አስተዳደሩ የወሰዳቸውን ዋና ዋና እርምጃዎች ይፋ አድርጓል፡- • አንደኛ፡ የሸማቾች ማኅበራት የምርት አቅርቦትና ጥራት እንዲያድግ 500 ሚሊዮን ብር የሚያዝ ተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቧል • ሁለተኛ፡ የደላሎችን ሰንሰለት ለማሳጠር በአዲሷ አበባ መግቢያ በሮች ላይ አምራችና ሸማችን በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላትና የእሑድ ገበያዎች በሰፊው ይስፋፋሉ። • ሦስተኛ፡ የአከራይና ተከራይ ግንኙነት በሕግና በውል ስምምነት ብቻ እንዲመራ ይደረጋል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለውም፣ ሕገወጥና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጠንካራ የሕግ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸው፤ ኅብረተሰቡ አስተዳደሩ ባመቻቻቸው የሸማቾች ማኅበራትና የእሑድ ገበያዎች በመገበያየት ራሱን ከሕገወጥ ነጋዴዎች እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል። ዜጎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥማቸው በቂ ማስረጃ በመያዝ ለከተማ አስተዳደሩ ሪፖርት እንዲያደርጉና ያልተረጋገጡ ወሬዎችን ከመሰራጨት እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።