← All news
News Oct 21, 2026 · 17d ago

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል "ምንም ዓይነት ቀውስ የለም" - ኤርትራ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ አምባሳደር ሶፊያ ተስፋማርያም፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ምንም ዓይነት «ቀውስ» አለመኖሩን ለአሜሪካ ዲፕሎማቶች መገለጻቸው ተሰማ። አምባሳደሯ ከአሜሪካ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ዋሽንግተን እና ዓለም አቀፍ አካላት በኤርትራ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት ላይ የተደቀኑ ሥጋቶችን በትኩረት እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርበዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ሁለቱ ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ የእርስ በእርስ የክስ ልውውጥ ያደረጉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የኤርትራ ኃይሎች በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ አካባቢዎች «ሙሉ ወረራ» ፈጽመዋል ስትል ከሰሳለች። ኤርትራ በበኩሏ ይህንን ክስ ውድቅ አድርጋ አዲስ አበባ ወደ ቀይ ባህር በር ማግኘት ላይ ያተኮረ የጦርነት ዛቻ እና የሉአላዊነት ጥሰት እየፈጸመችብኝ ነው ስትል ለአጭር ጊዜም ቢሆን ውጥረቱ አሻቅቧል። በቀጠናው ሰፊ ግጭት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት ባየለበት በዚህ ወቅት፣ አምባሳደር ሶፊያ ኢትዮጵያ የኤርትራን ግዛት ለመጠቅለል ከሚያደርጉ ዛቻዎች እንድትቆጠብ አሳስበዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም አዲስ ግጭት እንዳይከሰት ለመከላከልና የሁለቱን ሀገራት ስጋቶች በኃላፊነት ለመፍታት በንቃት እንዲሠራ ኤርትራ ጥሪ አቅርባለች።