← All news
News Oct 21, 2026 · 17d ago

ቡርኪና ፋሶ የሞት ቅጣትን መልሳ አጸደቀች

ቡርኪና ፋሶ  የሞት ቅጣትን መልሳ ማጽደቋን የአገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር አስታዉቋል። አዲሱ የወንጀል ህግ በ2018 ተሰርዞ የነበረውን የሞት ቅጣት የሚመልስ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ባለስልጣናት እንደገለጹት፤ ይህ እርምጃ የህዝብን ሰላም ለማጠናከር፣ የሀገር ዋጋዎችን ለማስከበር እና ጸጥታን ለማሻሻል ያለመ ነው። የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ መሪነት በ2022 ከተደረገው መፈንቅለ መንግስት ወዲህ በወታደራዊ አስተዳደር ስር ትገኛለች፤ ትራኦሬ ባለፈው ዓመት የሞት ቅጣትን የመመለስ ዕቅድ እንዳላቸው ይፋ አድርገው ነበር። በሞት የሚያስቀጡ ወንጀሎች ሽብርተኝነት፣ስለላ፣ክህደት አባትን ወይም እናትን መግደል እና ለሞት የሚዳርጉ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ወይም የተከለከሉ ምርቶችን ማስገባት መሆናቸዉ ተገልጿል፡፡ ውሳኔው በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል የተባለ ሲሆን፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት የሞት ቅጣትን እንዳይመልስ አሳስቦ ነበር። በቡርኪና ፋሶ የመጨረሻው የተመዘገበ የሞት ቅጣት የተከናወነው በ1988 ነበር። ይህ ውሳኔ በሀገሪቱ የወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ ትልቅ ለውጥ የሚያሳይ ሲሆን፤ በሰብዓዊ መብቶች እና በሞት ቅጣት አፈጻጸም ላይ አዲስ ጥያቄዎችን አስነሷል።