“ህወሓት ከ800 በላይ ተሽከርካሪዎችን ይዞ ወደ ኤርትራ መሸሹ ለትግራይ ሕዝብ ያለውን አቋም ያሳያል”-ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ
የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የጸጥታና ሰላም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ በቅርቡ በትግራይ የተፈጠረውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ህወሓት ከ800 በላይ ተሽከርካሪዎችንና ሌሎች ንብረቶችን ይዞ ወደ ኤርትራ መሻገሩን ገልጸዋል። ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር እንደተናገሩት፣ ይህ እርምጃ ቡድኑ ከትግራይ ሕዝብ ጥቅምና ደህንነት ይልቅ ለራሱ ህልውና ቅድሚያ መስጠቱን የሚያሳይ ነው። ቡድኑ በራሱ አቅም መቆም እንዳልቻለና ወደ ኤርትራ በመሄድ የውጭ ድጋፍ ለማግኘት መሞከሩንም ጠቁመዋል። ባለሥልጣኑ አክለው እንደገለጹት፣ ቡድኑ በአካባቢው በሌለበት ወቅት ደጋፊዎቹ የተለያዩ መረጃዎችን በማሰራጨት ሕዝቡን ለማደናገር ሙከራ ቢያደርጉም፣ የቡድኑ አቋም በተግባሩ መገለጡን ተናግረዋል። በተለይም ሕዝቡና ወጣቱ ተጨማሪ ጦርነት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል። ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር የቡድኑ ወታደራዊ አቅም መዳከሙን በመጥቀስ፣ ከዚህ በፊት የነበረው የጦር አቅም እና አሁን ያለው ሁኔታ በእጅጉ እንደሚለያይ ገልጸዋል። በትጥቅ መታገል ከመቀጠል ይልቅ ወደ ሰላማዊ መፍትሔ መምጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በዚህ መሠረት፣ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የትጥቅ ትግልን በመተው ሰላማዊ አማራጭን መከተል የሁሉም ወገን ኃላፊነት መሆኑን ብርጋዴር ጄኔራሉ ጠቁመዋል።