← All news
News Oct 20, 2026 · 18d ago

“የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላምና ልማት ነው”- ብ/ጄኔራል ገብረእግዝአብሔር በየነ

የትግራይ ክልል ሕዝብ የሚፈልገው ሰላምና ልማት እንጂ ዳግም ጦርነት እንዳልሆነ የክልሉ የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የጸጥታና ሰላም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዝአብሔር በየነ (ወዲ አንጥር) ገለጹ። ብርጋዴር ጄኔራሉ እንደገለጹት፣ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ጦርነቱን ቢያቆምም፣ ሕወሓት ለዳግም ጦርነት ሲዘጋጅ በመቆየቱ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ፈቃደኛ አልነበረም። በዚህም የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ሰላማዊ ሕይወት የሚመልሰው የDDR መርሃ ግብር በጥርጣሬ በመታየቱ ሳይተገበር መቆየቱንና ወጣቶች ከዚህ የሰላምና የልማት ዕድል መጠቀም እንዳልቻሉ ተናግረዋል። ሕወሓት ወጣቶችን ወደ ሌላ ወታደራዊ ግጭት በማስገባት ክልሉን ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጓል ያሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ በርካታ ቁስለኛና ተፈናቃይ ወጣቶች እንዳሉና የትምህርት ዕድላቸውን ያጡም እንዳሉ ጠቁመዋል። ወጣቶች ጊዜያቸውን በውትድርና ከማሳለፍ ይልቅ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሰው ሕይወታቸውን እንዲገነቡም ጥሪ አቅርበዋል። የDDR መርሃ ግብር ለዘላቂ ሰላምና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ መሆኑን ያስረዱት ብርጋዴር ጄኔራሉ፣ በተጨማሪም ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ እንደማይወክል፣ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል ክልሉን ከሚጎዱ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቷል እና ሀብት ዘርፏል የሚሉ ክሶችን አንስተዋል። አሁን ላይ ሕዝቡም ሆነ ወጣቱ ጦርነት እንደማይፈልግ ገልጸው፣ በኃይል የማሸነፍ ሐሳብ ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር እንደማይጣጣም አመልክተዋል።