← All news
News Oct 20, 2026 · 19d ago

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በግዳጅ ተመልምለው ወደ ጦርነት የገቡ የትግራይ ወጣቶች ከጦርነት ወደ ልማት እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግዳጅ ተመልምለው ወደ ጦርነት የገቡ የትግራይ ወጣቶች ሕይወታቸውን ለጦርነት ከማዋል ይልቅ ወደ ሰላማዊ ሕይወትና ልማት እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በእርስ በርስ ጦርነት ከሁሉም በላይ እየተጎዳ ያለው የትግራይ ወጣት መሆኑን ገልጸዋል። የጦርነት ውሳኔ የሚያስተላልፉ የህወሓት መሪዎች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከጦርነቱ ጉዳት ለመጠበቅ ሲጥሩ፣ ወጣቶች ግን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለሥነ ልቦና ጉዳት እየተጋለጡ እንደሆነ ተናግረዋል። በመቐለና በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች በጦርነት አካላቸው የጎደለና በከባድ የኑሮ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን በማስታወስ፣ ወጣቱ ለሌሎች የፖለቲካ ጥቅም ሲል ሕይወቱን ማጣት ወይም አካሉን ማጉደል እንደሌለበት አሳስበዋል። የትግራይ ወጣቶች በተለያዩ የትጥቅ ትግሎችና ግጭቶች የደረሰባቸው ጉዳት የጥፋት ዑደቱ እንዲቆም የሚያሳስብ መሆኑንም ጠቁመዋል። ወጣቶች ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን ለልማት እንዲያውሉ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቦታቸው በዩኒቨርሲቲዎች፣ በንግድ፣ በግብርናና በፋብሪካዎች ውስጥ እንጂ በጦር ሜዳ ላይ እንዳልሆነ ገልጸዋል። የትግራይ ወጣቶች መሣሪያ ከመያዝ ይልቅ ኮምፒውተር በመጠቀምና በሥራ በመሰማራት የራሳቸውንና የክልሉን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዲገነቡ ጥሪ አቅርበዋል። በመጨረሻም ታጣቂ ወጣቶች መሣሪያቸውን በማስቀመጥ በሰላም ወደ ትጥቅ ማስፈታት፣ ተሃድሶና መልሶ ማቋቋም (DDR) ሂደት እንዲገቡና በትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።