← All news
News Oct 20, 2026 · 19d ago

ኢትዮጵያ ለ15 ወራት ተቋርጦ የቆየውን ወደ ኳታር የስጋ ኤክስፖርት ማስጀመሯን ገለጸች።

ኢትዮጵያ ለ15 ወራት ተቋርጦ የቆየውን ወደ ኳታር የሚደረግ የስጋ ኤክስፖርት ከጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም. ጀምሮ ዳግም ማስጀመሯን የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን አስታወቀ። የባለሥልጣኑ የእንስሳት ምርት ሬጉላቶሪ መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ዶ/ር አያሌው ሹመት እንደገለጹት፣ ኳታር በኤክስፖርት መስፈርቷ ላይ ያካተተችውን ተጨማሪ ነጥብ ለማሟላት ባለመቻሉ ኤክስፖርቱ ተቋርጦ መቆየቱን ገልጸዋል። እገዳው በኢትዮጵያ ላይ ብቻ የተጣለ እንዳልነበረ ያነሱት ዶ/ር አያሌው፥ በግብርና ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና ከኳታር ኤምባሲዎች ጋር በተደረጉ ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች መፍትሔ መገኘቱን ተናግረዋል። እንስሳቱ ከመታረዳቸው በፊት በሰበታ እንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት አማካኝነት የደም ናሙና ተወስዶ የላቦራቶሪ የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ በመደረጉ ወደ ውጭ መላክ መጀመሩን ነው ያብራሩት። ኳታር ኢትዮጵያ ስጋ ከምትልክባቸው ሦስተኛዋ ትልቅ የገበያ መዳረሻ መሆኗን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በቀጣይ ወደ ቻይና ገበያ ለመቀላቀል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም አቀፍ ንግድ መረጃ ቋት መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2023 ብቻ ወደ ኳታር የላከችው የሥጋ ምርት 3.69 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያስገኘ ነው።