በህፃናት አጥንት እና መገጣጠሚያ ላይ የሚከሰት ኢንፌክሽን በ8 ሰዓታት ዉስጥ ህክምና ካላገኘ የመገጣጠሚያ መድረቅን ያስከትላል ተባለ
ህፃናት ላይ ለሚከሰት የአጥንት እና መጋጣጠሚያ ችግር ዋነኛ ዉ ምክኒያት ኢንፌክሽን ቢሆንም የተመጣጠነ ምግብb አለማግኘትም ለዚህ አይነቱ ችግር እንደሚያጋልጣቸው ለብስራት ሬዲዮ የተናገሩት በሳይንስ አምባ የአጥንት እና መገጣጠሚያ እስፔሻሊቲ ክሊኒክ የአጥንትና መገጣጠሚያ ስፔሻሊስት ዶክተር የአብ ሙላት ናቸዉ ። በህፃናት አጥንት እና መገጣጠሚያ ላይ የሚከሰት የአጥንት ኢንፌክሽን በመጀመሪያዎቹ ሰባት እና ስምንት ሰዓታት ዉስጥ ህክምና ካላገኘ የመገጣጠሚያ መድረቅ በማስከተል እንቅስቃሴን በእጅጉ እንደሚገድብ ዶክተር የአብ አክለዋል ። በተጨማሪም በህፃናት የአጥንት እድገት ላይ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር የማጠር ፣የመርዘም ወይም የመጣመም ችግርንም ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል ። በአጥንት እና መገጣጠሚያ ላይ የሚከሰት ኢንፌክሽን እንደየህፃናቱ ዕድሜ እና የኢንፌክሽኑ መጠን የሚለያይ ቢሆንም ወደ ሰዉነት ተሠራጭቶ ለሞትም ሊያጋልጣቸዉ ይችላል ተብሏል ።በዚህም የተነሳ ወላጆች ኢንፌክሽን ሲኖር ልጆችን በቶሎ ወደ ህክምና ተቋም በመዉሰድ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለባቸዉ ስፔሻሊስቱ አሳስበዋል ። በመዉደቅ ምክኒያት የሚከሰት ስብራት እና ዉልቃት ሌላኛዉ በህፃናት ላይ ለሚከሰት የአጥንት እና መገጣጠሚያ ህመም መንስኤ ሲሆን በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ከተቻለ ያለ ቀዶ ህክምና በቀላሉ መዳን እንደሚቻል ተጠቁሟል ። ህፃናት ሲወድቁ ወደ ህክምና ተቋማት ከመዉሰድ ይልቅ ወደ ባህላዊ ህክምና የመዉሰድ አዝማሚያ መኖሩን የሚገልፁት ዶክተር የአብ ይህም በቀላል ህክምና መዳን እየቻሉ ቀዶ ህክምና ለማድረግ እንደሚገደዱ ገልፀዋል ።